ሰሞኑን በጎንደር በተለይም በጎንደር ከተማ እየተንሰራፋ የመጣውን የሥርዓት አልበኝነት እና ሕገወጥ ተግባራት መበራከት አስመልክቶ የተለዩ ሃሳቦች ሲሰነዘሩ ሰንብተዋል። በዚህ መነሻ ተከታታይ ክፍል ያለው ጽሑፍ ወደናንተ አደርሳለሁ፡፡ የጽሑፉ ዓላማ በጎንደር ከተማና በአካባቢው ሥርዓት አልበኝነት ለምን ሊስፋፋ ቻለ የሚለውን በግለሰብ ግንዛቤ መጠን በማስቀመጥ ውይይት እንዲደረግበት ምክኒያት መሆን ነው።
ሥርዓት ጠልነትና መነሻ ባህሪያቱ
ሥርዓት ጠልነት ወይም አናርኪዝም ገዥዎች ወይንም መንግሥታት መዋቅሮቻቸውን በመጠቀም ሕዝብን ይመዘብራሉ፣ ይበድላሉ የሚል መነሻ ያለው ሲሆን፤ መንግሥት፣ የመንግሥት መዋቅር ወይም የአስተዳደር እርከን እንዲሁም ሌሎች እኩል ተጠቃሚነትን እና ፍትኃዊነትን (Equity and Justice) የሚያጓድሉ በመሆኑ አስፈላጊ አይደሉም፤ ሕዝብ መተዳደር ያለበት በራስ ገዝነት ፣ በተጓዳኝነት፣ በመተጋገዝ፣ በአብሮነት እና ሕዝቡ በሚውስዳቸው ቀጥተኛ ተግባራት ነው የሚል መነሻ ያለው ነው።
በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰሩ ዲቪድ ዲ’አማቶ ‹አናርኪዝም መነሻው ጭቆናን መጥላት የሆነ በመንግሥት መዋቅር ሥር ያለን ሁሉ የመቃወም፣ የማማረር እና ሕገ-ልቦናን ተከትሎ የመተዳደር ዝንባሌ እንደሆነ› ይብራራሉ፤ አናርኪዝም የመንግሥትን አስተዳደርና መዋቅር ተጠቅሞ እኩይ ተልዕኮዎችን የመፈፀምና ወንጀል ከፈፀሙ በኋላ የተለያዩ ቡድኖችን በማቋቋም በሕዝብ ውስጥ የመደበቅ እንቅስቃሴን የሚጨምር መሆኑንም ያክላሉ። በዚህ ትርጓሜና ግንዛቤ መሰረት በጎንደር ከተማና አካባቢው ሕዝቡን በጽኑ ያማረረና ሰዎችን አግቶ ከፍ ያለ ገንዘብ እስከመቀበል እና ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ ታጋቹን እስከመግደል የደረሰው ዓይን ያወጣ ወንጀለኝነት በአካባቢው የለየለት የአናርኪዝም ሰንኮፍ ያለ መሆኑን መገመት ያስችላል። በርግጥ ከእገታ ጋር ተያይዞ የሚታየው የማኅበረ-ፖለቲካ ቀውስ መነሻው፣ ትህነግ ለሽብር ተልዕኮ ያሰማራው የቅማንት ኮሚቴ የሚባለው ወንበዴ ቡድን ሲሆን፤ ቡድኑ የአካባቢውን ሕዝብ እረፍት ለመንሳት (Social unrest) ሆን ተብሎ የተፈጠረ ቢሆንም በሂደት ሌሎችም ተቀላቅለውት የሰው ልጅ እገታን የገቢ ማግኛ ምንጭ አድርገውት ታይቷል፡፡ በሁለቱም መንገድ ሥርዓት አልበኝነት ስለመንገሡ ግን ጥርጥር የለውም፡፡
ለማኅበረ-ፖለቲካዊ ቀውሱ አንደኛው ሁኔታ ይህ መሆኑን እያሰመርንበት፣ ጎንደር ላይ ሲታዩ የከረመት ሌሎች ውጥረቶች መነሻቸው ሥርዓቱና የሥርዓቱ መዋቅር በሕዝቡ ላይ የሚያደርስበትን ግፍ በመንገፍገፍ፣ በመጠየፍ እና በመሳቀቅ ‹ከእምቢተኝነት› የመጣ ሥርዓት ጠልነት ነው። ጎንደር በሥርዓቱ የተንገፈገፈ/አምርሮ የጠላው/ መሆኑን ያወቁ ጥቂት ችግር ቸርቻሪ ነጋዴዎች ደግሞ ሁኔታውን በግልፅ የሥልጣንና የጥቅም ምንጭ አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። በጎንደር የወጣቱ ትግል ከረጅም ዓመታት ጊዜ ጀምሮ እንዴት እንደተጠለፈ እና አካባቢው ለአናርኪስቶች ምቹ እየሆነ እንደመጣ እንዲሁም አጠቃላይ የጎንደርን ማሽቆልቆል የወለዱ ነገሮችን እንመልከት።
(ሀ) ድርጅታዊ ክህደት
በዚህኛው ንዑስ ርዕስ በጎንደር ወጣቶችና ታጋዮች ላይ ያላማቋረጥ እየዘነበባቸው ያለውን ድርጅታዊ ክህደት እንመለከታለን፡፡ የዘውዳዊውን ሥርዓት ለመገልበጥ በተደረገው እንቅስቃሴ እና ሁሉም ወጣት በየፊናው የሥርዓት ለውጥ ናፋቂ ሆኖ በተለያዬ አግባብ በመሳሪያም ያለመሳሪያም በሚያደርገው ትግል ውስጥ የጎንደር ወጣቶች ያልተሳተፉበት እንቅስቃሴ አልነበረም። ይሁን እንጅ ዘውዳዊ ሥርዓት ወድቆ ደርግ ሲመጣ የጎንደር ወጣቶች ውለታ መረሸን፣ መሰደድና በገደል መወርወር ሆነ። በዚህም ደርግ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ የጎንደር ልጆችን ረሽኗል፤ በቀይ ሽብር እርምጃ አርግፏቸዋል (ከሰለባዎች ውስጥ አንዷ አክስቴ ስትሆን ጎንደር ቀበሌ 09 ተረሽናለች)። የጭካኔ ዝናቸው በኢትዮጵያ ከዳር እስከዳር ይሰማ የነበረው መላኩ ተፈራና ገብረ ሕይዎት ከጎንደር እናቶች እቅፍ ልጆቻቸውን ነጥቀዋል፤ ከቀይ ሽብር የተረፉትን እንዲሳደዱ አድርገዋል። መንገድ ለመንገድ የተሰውትንና መድረሻቸው ያልታወቀውን ሳይጨምር በመተማ በኩል አምልጠው አሜሪካ የገቡት ጎንደሬዎች ቁጥር ብቻ ሃያ ሺህ የሚሻገር እንደሚሆን ይገመታል። ይህ የአረመኔዎች የግፍ ቀንበር ጎንደር የትውልድ ክፍተት እንዲፈጠርባት አድርጓል። በወታደራዊው መንግሥት ቃታ በወደቁ ልጆቹ ምክኒያት እና እንደ ሊማሊሞ ባሉ ገደላማ ስፍራዎች በፍጥኝ (ወደኋላ) እየታሰሩ ቁልቁል በተወረወሩት ልጆቹ ምክኒያት የጎንደር ሕዝብ የደርግን የግፍ አገዛዝ በመቃወም ከፊት ሆኖ ተዋግቷል። ሃዘናቸው በቅጡ እንዳይወጣ እግድ የተጣለባቸው የጎንደር እናቶች ‹አይዞህ ልጄ› እያሉ ስንቅ እየቋጠሩ ልጆቻቸውን በረሃ መሸኘታቸው የምሬቱን ልክ ሊያሳይ ይችላል።
በተለምዶ የ60ዎቹ ትውልድ እየተባለ የሚጠራው እና ከዘውዳዊው ሥርዓተ-መንግሥት ውድቀት በኋላ የቀዩ መጽሐፍ ሸምዳጅ፣ የግራ ዘመም ሶሻሊዝም ርዕዮት አነብናቢ ሁኖ ራሱን የገለጠው ያ-ትውልድ፤ የሶሻሊስት ሥርዓት ፅንፈኝነት ውድድር ውስጥ ገብቶ እንደ አሸን ድርጅት የፈለፈለው ወጣት በሙሉ በደርግ ጡንቻ ተገፍቶ በርሃ ሲወርድ ተገን ያደረገው በዋናነት የሰሜኑን ሕዝብ ሲሆን፤ የጎንደር በርሃዎችን እና የጎንደር ገበሬዎችን ጓዳዎች መጠቀሚያ ከተደረጉት መካከል ናቸው። ጀብሃን ጨምሮ በተሓህት፣ በኢህአፓ፣ በመኢሶ፣… ወዘተ በመሳሰሉት አደረጃጀቶች ውስጥ የጎንደር ልጆች ያልነበሩበት ማግኘት ይከብዳል። የኋላ የኋላ በለስ ቀንቶት ወንዝ እንዳመጣው ግንድ ከሁሉ በላይ ልቆ መታየት የጀመረውን የትህነግ (ህወሓት) ማኅደር ብንፈትሽ እንኳን ከ7ቱ መስራቾች አንዱ የሆነውን የጎንደር ድብባህር ተወላጁን አብተውን እናገኘዋለን፡፡ እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን፣ እነ ታጋይ ሙሉዓለም አበበን መጨመርም ይቻላል። የተወሰኑ የጎንደር ወጣቶች ትህነግን የተቀላቀሉት የትህነግ ‹ፀረ አማራ›፣ ‹ፀረ-ኢምፔሪያሊዝም› ማንፌስቶ በመቀበል እና አማራን ለማጥፋት በመስማማት ሳይሆን የደርግን ሥርዓት አምርሮ ከመጥላት እንደነበር ከ1970ዎቹ የሚጀምረውን የሻለቃ ሰፈር መለሰን የአራት አሥርት ዓመታት ተጋድሎ በአስረጅነት ማቅረብ ይቻላል። (ሻለቃ ሰፈር ድኀረ-1983 ትህነግን በመታገል ስሙ ከፊት የሚነሳ አርበኛ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም በማይጠምሪ ግንባር ሕዝባዊ ጦሩን እየመራ ይገኛል) ይሁን እንጅ ትህነግ በአካባቢው አጠራር ተሓህት በነበረችበት ጊዜ ከፊት ሆነው መሠረት ያስያዟት እና የደርግን የግፍ አገዛዝ በመገርሰስ አብረዋት የተሰለፉትን እነ አብተውን ስትክድ፣ ሌሎቹን ስታስወግድ ገና በአስራ ሰባት መርፌ የጠቀመችውን ቁምጣዋን አላወለቀችም ነበር።
የወልቃይትን ሰዎች በጅምላ ስትቀብር እና ለም መሬታቸውን ዘርፋ ለመበልፀግ ውጥን ስትነድፍ ለምን ያሉ ጎንደሬዎችን በቁም እስር፣ ከማዕረግ ዝቅ በማድረግ ብሎም አድራሻቸውን በማጥፋት ብዙ ግፍ የፈፀመችው እዚያው በርሃ እያለች ነው። ትህነግ አዲስ አበባ ከገባች በኋላ ደግሞ እንኳን የጎንደር ውለታ አለብኝ ልትል ጭራሽ በተቃራኒው ፀረ-ጎንደር ሆና መሬት መቀማት፣ ሕዝብ ማፈናቀል፣ የዘር-ማፅዳት ማድረግ እና ጎንደር ማግለል በይፋ ፈፅማለች። ወጣትነታቸውን የደርግን ሥርዓት በመታገል ያሳለፉ የቀድሞ የኢህዲን ወታደሮች ሳይቀር የመከዳት ስሜት እንዲያድርባቸው አድርጓል። በአንድ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩና በበረሃው ትግል ጊዜ ከእነ መለስ ዜናዊ ጋር አብረው የታገሉ አንድ የጎንደር ሰው አግንቼ ስለሁኔታው ጠይቄያቸው ነበር፤ መልሳቸው የመከዳት ስሜት እንዳደረባቸው የሚያሳብቅ ሲሆን በአጭሩ ይኼ ይገባናል (ባ ትጥበቅ) ብለን አልበነበረም የታገልነው ብለውኛል። ትህነግ ዘረኛ ሥርዓት አንግሶ አገር ሲበጠብጥ እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ፀረ-ትህነግ ትግል ሲያደርጉ የጎንደር ወጣቶች በሰላማዊ መንገድም በጠመንጃም ትግሉን ተቀላቅለው መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ እየከፈሉም ነው። የቀድሞው አርበኞች ግንቦት 7 (የአሁኑ የኢዜማ ውህድ) በርሃ ወርጀ ለነፃነት እየታገልኩ ነው በሚልበት ወቅት መጠቀሚያ ካደረጋቸው አካባቢዎች ውስጥ ጎንደርን በተለይ አርማጭሆን ነበር። ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ሲሰጠው የነበረው ሰሜን ዕዝ የጎንደር ልጆች ደም በከንቱ የፈሰሰበት ነው። በየቦታው በሚነሳው ተጋድሎ ሁሉ ሰሜን ዕዝ አለበት በመባሉ በግንቦት 7 ስም የጎንደርን ሕዝብ እስከአፍንጫው ከታጠቀ ጨካኝና አረመኔው የትህነግ ቡድን ጋር ሲዋጋ ኖሯል። ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻቸው ጋር በኤርትራ በርሃ ከወደቁት በርካታ የጎንደር ልጆች በተጨማሪ የወያኔ እስር ቤቶች በጎንደር ልጆች የተሞሉ እንደነበሩ አማራም ያልሆኑ ሰዎች ጭምር ምስክርነት የሰጡበት የአደባባይ ምስጢር ነው። በጎንደር ልጆች ላይ የተፈፀመን ኢ-ሰብዓዊ አረመኔያዊ ድርጊት ከለውጡ በኋላ አማራ መገናኛ ብዙኃን ዘግቦታል። ይህ በአርበኞች ግንቦት 7 ስምና ሰበብ በጎንደር ላይ የተፈፀመ ግፍ ነው። የግንቦት 7 ሰዎች ግን የጎንደርን ውለታ የመለሱት በእነርሱ ምክኒያት የቁም ስቃይ የተቀበሉትን እነ ቀለብ ስዩምን እንደ ጎንደር ሰው ካልሆንሽ … እናግዝሻለን (በእነሱ አጠራር የጎንደር ሰው ማለት ለሀቅ ፊት ለፊት የሚጋፈጥና የሥርዓቱን ጉዶች የሚዋጋ ማለት ነው፤ ይህ ግን
ለአንዳንድ ለኢዜማ ሰዎች የተላላኪነት ፖለቲካ ተስማሚ አልነበረም) በማለት መስዋዕትነት ከከፈለችበት ድርጅት ተገፍታ እንድትወጣ ማድረግ ነው፤ ዝርዝሩ በፍትሕ መጽሔት ላይም ወጥቷል። በዚህ ትግልም የጎንደር ወጣቶች ያተረፉት መከዳትን ነው።
ከዘውዳዊ ሥርዓተ-መንግሥት መገርሰስ በኋላ የመጣው በጎንደር ወጣቶች ትግል ላይ የሚደረገው ድርጅታዊ ክህደት በብልጽግና መንግሥትም እንደቀጠለ ነው። በ2008 ዓ.ም ጀምሮ ወያኔን በማስወገድ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በውጭም በውጥም ያሉ የጎንደር ወጣቶች አስተዋፅኦ አድርገዋል። ለውጥ መጣ ከተባለባት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ግን የጎንደር ወጣቶች እየተገፉ የት እንደነበሩ የማይታወቁ የአዴፓ/ብልጽግና ወዳጆች የትግሉ ፊታውራሪ ሆነዋል። ከጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ትህነግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በትጥቅ ትግል ለመደምሰስ እየተደረገ ባለው ጦርነት ውስጥ የጎንደር ወጣቶች ሚና ምን እንደሆነ በተግባር እየተመለከትነው ያለነው ጉዳይ ስለሆነ መዘርዘር የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም። ወሮታቸውና መስዋዕትነታቸው በምን አግባብ እንደተያዘ እና በአጠቃላይ መከፋት እንደፈጠረም እንዲሁ እያየነው ያለ ጉዳይ ነው። ይህ ድርጅታዊ ክህደት እና የጎንደር ገበሬና ወጣቶች መሳሪያ ተሸካሚ እና አንጋሽ (King Makers) እንጅ በወርድና በቁመታቸው ልክ ሥልጣን ተጋሪ አለመደረጋቸው ወጣቶቹ ሥርዓት ጠል እንዲሆኑ ያደረጋቸው ይመስላል።
ለጎንደር ሕዝብ ሸክም የሆኑ የማፍያ ስብስቦች ትጥቅ ያገኙበት ምክኒያት ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት የመከዳት ብሶት በአካባቢው ስላለ አካባቢውን በራስ ትግል ለመቆጣጠር በሚደረግ እንቅስቃሴ ሰበብ ነው። ሁኔታውን በደምብ የሚያውቁት የአካባቢው ካድሬዎች ደግሞ ነገሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ስላዩት ለግል ጥቅምና ሥልጣን ማግኛ ለማዋል እየሞከሩ ይገኛሉ፤ ሥርዓቱ ገፍቶኛል የሚለውን ወጣት ቁስል በመነካካት ቁማር ይጫዎታሉ። ለሕዝቡ ‘ሕገወጥነትን እናጠፋለን ችግሩን እንቀርፋለን’ እያሉ ከወሮበሎቹ ጋር ደግሞ እየተሻረኩ አካባቢውን በጥብጠዋል፤ አናርኪዝም እንዲስፋፋ አድርገዋል። በወንዜነት እና በሰፈር እየተደራጁ ከጀርባቸው ወሮበሎችን ጠባቂ አድርገው እየመደቡ ከቅጥረኛው የቅማንት ኮሚቴ የወረሱትን የሰው ልጅ እገታ ወንጀል ውስጥ እስከ መግባት ድረስ በደረሰ ከባድ አዘቅት ተዘፍቀዋል። ሲጠቃለል ብሶት ትግልን፣ ትግል መከዳትን፣ መከዳት ብስጭትን፣ ብስጭት ለጥቅመኞች ሰላባ መሆንን፣ የጥቅመኞች ሰለባነት አናርኪዝምን ወልደዋል።
(ለ) ጎንደር በልማት ተጠቃሚ አለመሆን
በተራ ቁጥር (ሀ) በጎንደር ወጣቶችና ታጋዮች ላይ ያላማቋረጥ እየዘነበባቸው ያለውን ድርጅታዊ ክህደት ማሳያዎችን እያነሳን ተመልከተናል፡፡ ይህም ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ለተፈጠረው የሥርዓት ጠልነት መነሻ ምክንያት ስለመሆኑ ሞግተናል፡፡ በዚህኛው ክፍል ደግሞ ለቀጠለው የሥርዓት ጠልነት ተጨማሪ መነሻ ምክንያት የሆኑትን ከመሠረተ ልማት ተጠቃሚነት መገለልን እና በአማራ ብሔርተኝነት አነሳስና አካሄዱ ሀቅን የሸሸ፤ የሴራ ፖለቲካው የፈጠረበትን ስብራትና የጎንደርን ችግር መባባስ እንመለከታለን፡፡
ጎንደር በቆዳ ስፋት ትልቅ ሲሆን፤ በሕዝብ ብዛት ደግሞ ከትግሬ፣ ከአፋር፣ ከሶማሊ፣ ከጋምቤላ፣ ከሐረሪ፣ ከጉሙዝ ክልሎች የሚበልጥ ቢሆንም እንደ ወርዱና እንደ ቁመቱ የልማት ተጠቃሚ ያልሆነ አካባቢ ነው። አማራ ክልል እና በአጠቃላይ የአማራ ሕዝብ ታቅዶና ታስቦ ስትራቴጅካዊ በሆነ መልኩ ከሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲገለል መደረጉ የሚታወቅ ነው። በአንጻራዊ ሁኔታ አማራ ክልል በሚባለው የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ደግሞ ሆነ ተብሎ ፍትኃዊ ተጠቃሚነት እንዳይኖር በማድረግ የአማራውን ሕዝብ የመነጣጠልና በአንድነት እንዳይቆምና ጠላቱን እንዳይዋጋ ለማድረግ በተሰራው የትግሬ ልሂቃን ተንኮል ጎንደር በግልፅ የልማት ተጠቃሚ እንዳይሆን ተደርጓል፤ የድሃ ድሃ ሆኗል በወያኔ መዝገበ ቃላት።
ጎንደር በመሠረተ-ልማት (መንገድ፣ ውኃ፣ መብራት ወዘተ) በልዩ ሁኔታ እንዲጎዳ ተደጓል። በጎንደር ክፍለ-ሃገር በሚገኙ አምሥት ዞኖች መካከል በሃያ ስምንት ዓመት ውስጥ አንድ እንኳን ሰብስቴሽን አልተገነባም፤ አለመገንባቱ ብቻ ሳይሆን በአስቸኳይ ከመገንባት ይልቅ የተገነባ ሳብስቴሽን አለመኖሩ እየተጠቀሰ ለሕዝቡ እንዲነገረውና በተበዳይነት እንዲንገበገብ ጭምር ተደርጓል። በኢኮኖሚ፣ በጤና እና በትምህርት ጎንደር የመጨረሻው መጨረሻ ነው። በኢንዱስትሪ ግንባታ በኩል ኋላ የቀረ ነው፤ ከአማራ ክልል ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርክ የሌለው ብቸኛው አካባቢ ጎንደር ነው። በአንጻሩ ጎንደር እንደሌላው ሁሉ የራሱ ፀጋዎች ያሉትና ለውጭ ምንዛሬ ኤክስፖርት የሚደረጉ ጥሬ ሃብቶች ያሉበት አካባቢ ነው።
በተለያዩ ድርጅቶች ስም እና ሽፍታ በሚል ቅፅል ስም በርካቶች የተረሸኑበት፣ የተኮላሹበት፣ የተሰደዱበት ጎንደር ከመሳሪያ አንጋቹ ውጭ ያለው የሕዝብ ክፍል በሰው ሰራሽ ድህነት ውስጥ እንዲማቅቅ እና የሴፍቲኔት ጥገኛ እንዲሆን ልጆቹም ስራ አጥ ሆነው በየጎዳናው ሲያለቅሱ እንዲወሉ ወይም እንዲሰደዱ ተደርጓል። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ የጎንደር ወጣቶች የልማት ተጠቃሚ አይደለንም ብለው ጥያቄ እንኳን እንዳያነሱ እስከ አጥንት ሰብሮ የሚገባ ስም ይለጠፍባቸዋል። ለአማራ ሕዝብ እንታገላለን የሚሉ አካላት ራሱ ጎንደር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ አይደለም ሲባል ትህነግ ለሰራው በደል እነሱ ጎንደርን አግላችሁታል ተብለው የተከሰሱ ይመስል ደስ አይላቸውም፤ ደስ አይላቸውም ብቻ ሳይሆን ‹አማራ አጠቃላይ ተበድሏል ለምን ጎንደር ትላላችሁ› እያሉ የጎንደር ወጣቶችንና ታጋዮችን ያሸማቅቃሉ። ሕዝብ ግን ሁሉም ነገር አንጻራዊ መሆኑን ስለሚያውቅ ከአፍሪቃ አንጻር ኢትዮጵያ ደሃ መሆኗን፣ ከኢትዮጵያ ውስጥ ትህነግ ሆነ ብሎ አማራ ደሃ እንዲደረግ ማድረጉን፣ ከአማራ ክልል ውስጥ ደግሞ ጎንደር በስሌት ከኢኮኖሚ መገፋቱን አጥርቶ ያያል፤ ያውቃል። ይህ ጉዳይ የጎንደር ወጣትና ታጋይ በሥርዓቱ ላይ ጥላቻን እንዲያሳድር አድርጎታል። የጎንደር ወጣቶች በትግሉ ጊዜ ከሁሉ በላይ እየሞትን ተጠቃሚነት ሲመጣ ግን ዘውትር እንረሳለን የሚል መንገፍገፍ ያለበት አካባቢ ሆኗል።
አልማ ከሁለት ዓመት በፊት በባለሙያዎች አስጠንቶ ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት በአማራ ክልል ከሚገኙ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 86% የሚሆኑት ከደረጃ በታች መሆናቸውን አረጋግጧል። በጎንደር ዞኖች ውስጥ በተለይም በማዕከላዊና ሰሜን ጎንደር አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች በዳስ የተሰሩ ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ስንመለከት የክፍል ተማሪ ጥምርታው 1፡ 65 ሲሆን፤ የመምህር ተማሪ ጥምታው 1፡70 የደረሰባቸው የወረዳ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ የመጽሐፍ ተማሪ ጥምርታው 1፡4 እንደሚደርስ ታውቋል፡፡ በትምህርት ባለሙያዎች ምዘና መሠረት እነዚህ ጥምረታዎች የትምህርት ጥራቱን በእጅጉ ይጎዱታል፡፡ በሌላ በኩል በጎንደር ከተማ 96% የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸውን የከተማዋ ትምህርት መምሪያ በሰራው የዳሰሳ ጥናት አመላክቷል። በዚህ ሁኔታ እየተማሩ ያደጉ ልጆች የሕይወት ዕጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ዛሬ ላይ የቆምንበት ነባራዊ ሁኔታ ከበቂ በላይ አስረጅ ነው፡፡ የሁኔታው አሳሳቢነት ነገሮች በዚህ መንገድ እንዲቀጥሉ የማድረግ ፍላጎት ከክልልም ሆነ ከፌዴራል መኖሩ ነው፡፡
ከላይ የተዘረዘረውን ችግር የተረዱና የጎንደር ወጣትና ታጋይ ሥርዓቱን እንደሚጠላ ያወቁ አናርኪስቶች አጋጣሚውን ተጠቅመው በስሙ ለመነገድ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። በክፍል አንድ እንደተጠቀሰው በተለያዬ አግባብ በመደራጀት እና ብሶቱን በመጭመቅ የገቢ ምንጫቸው አድርገውታል። ከዚህም አልፈው ሕዝቡ በአቅጣጫ ሰሜን/ደቡብ ተባብሎ እንዲናከስ ሰፊ ጥረቶች አድርገዋል። ጠላትም ሆነ ካድሬው በሚፈጥረው ትርክት ሲጠላለፉ ኑረዋል፤ በመሀል ሕዝቡን ከልማት ተጠቃሚነት ገፍተው ወጣቱና ታጋዩ በሥርዓት ጠልነቱ እንዲቀጥል አስገድደውታል። ቅማንትነትን እንደፖለቲካ መሳሪያ የሚቆጥሩ ካድሬዎች ደግሞ ትህነግን ተገን በማድረግ ብሶትና ግጭት በመጥመቅ የራሳቸውን ትርክት ፈጥረው ዋነኛ አሸባሪዎች ሆነው ጎንደርን ሲያምሱ ከርመዋል፣ አሁንም እያመሱ ይገኛሉ፤ ከዞንም፣ ከክልልም፣ ከፌደራልም ያሉ ግጭት በመጥመቅ የተካኑ ደግሞ ያግዟቸዋል። ጎንደር ከኢኮኖሚ መገለሏን ምክኒያት በማድረግ የአናርኪዝም መፈንጫ የሆነችበት ሌላው መንገድ ይኼ ነው።
(ሐ) ሀቅን የሸሸ፣ የሴራ ፖለቲካ የፈጠረው ስብራት
እንደ ክርስቶፈር መስካቶ ትርጉም ብሔርተኝነት ማለት በአንዲት አገር የጋራ ሃሳብ ዙሪያ አንድነት ያለው ማንነት ከፍ ማለት ነው (Nationalism is the elevation of a unified identity around the shared concept of the nation: Christopher Muscato, University of Northern Colorado) ሲል ይገልጸዋል፡፡ ብሔርተኝነት የተቃውሞ ዝንባሌ ያለው ጽንሰ-ሃሳብ ሲሆን፤ ከአገር ባለቤትነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለውና የአገር ኅልውና መሠረትም ነው። በአጠቃላይ በምሁራን መካከል ብሔርተኝነት ከሁለት የተለያዩ ቅርጾች አንዱን ሊወስድ እንደሚችል የሚታመን ቢሆንም በርካታ የኅብረተሰብ ሳይንስ ተማራማሪዎች ከሁለት በላይ ብሔርተኝነቶች እንዳሉ ይጠቅሳሉ። እንደ ቀድሞው ፕሮፌሰርና የካናዳ ሊበራል ፓርቲ መሪ ሚካኤል ኢናቴፍ (Micheal Ignatieff) አገላለጽ የማንነትን መሠረት ያደረገ ብሔርተኝነት (ethnic nationalism) ወይንም የማንነት ብሔርተኝነት የጋራ ቋንቋ፣ ሀይማኖት፣ ሥነ-ልቦና ያለው ሕዝብ ወይንም ብሔር በጋራ ማንነቱ ከፍ ማለት ባለው ጥብቅ ሀሳብ ተመስርቶ የሚያንቀሳቅሰው የፖለቲካ አጀንዳ ነው።
በማንነት ላይ ያተኮሩ ብሔርተኝነቶች መንሥኤዎች ከማንነት መከበር፣ ከሐብት ክፍፍል፣ ከፖለቲካ ውክልናና ከማኅበራዊ ፍትሕ ጋር የተያያዙ ናቸው። መንሥኤዎቹ ከማኅበረሰቡ የቀን ተቀን ኑሮ ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው ህዝቡን ለማነሳሳትና ተቀባይነት ለማግኘት ጊዜ አይወስድባቸውም። በተመሳሳይ የአማራ ብሔርተኝነትም ተቀንቅኖ በሕዝብ ውስጥ እስኪሰርፅ ድረስ ሦስት ዓመት እንኳን አልፈጀበትም።
የማንነት ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ እንደ ማንኛውም እንቅስቃሴ ህፀፆች የሚኖሩት ሲሆን በተለይ በማንነት ብሔርተኝነት ስም የበላይነትን ለማስፈን ወይንም ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ሸፍጥ ሲኖር ለከፋ ጉዳት በተለይም ለአናርኪዝም ማቆጥቆጥ በር እንደሚከፍት በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ። የማንነት ብሔርተኝነት የበላይነት ስሜት ባላቸው ወይንም በስልጣን ጥማትና ሴራ ውስጥ በተዘፈቁ ቡድኖች ሲጠለፍ አደገኛና አጥፊ እንደሚሆን ምሳሌ ጠቅሶ ማሳየት ይቻላል።
የምስራቅ አውሮጳ አገር ጆርጅያ የማንነት ብሔርተኝነትን ተጠቅማ ከሶቪዬት ኅብረት አገዛዝ ራሷን ነጻ ያወጣች ቢሆንም የበላይነት የሚሰማቸው ቡድኖች (ብሔሮች) የሩሲያን መንግሥት እንደ ከለላ በመጠቅም አገራዊ አመለግባባትና ግጭት እንዲሁም አናርኪዝም እንዲፈጠር እያደረጉ ይገኛል። በጆርጅያ ግዛት ውስጥ ሦስት ብሔሮች ያሉ ሲሆን እነርሱም አብኻዚያ (Abkhazians)፣ ኦስሺያ (Ossetians) እና ቲቢሊሲ (Tbilisi) ናቸው። የብላድሚር ፑቲን መንግሥት አብኻዚያኖችንና ኦስሺያኖችን በጥቅም በመደለል ቲቢሊሲዎች ጆርጂያን እየተጠቀሙባትና እየመጠመጧት ነው የሚል ትርክት በመፍጠር የጆርጅያን አንድ አምስተኛ ግዛት ለመያዝ የበቃ ሲሆን፤ በአገሪቱ ውስጥ በብሔሮች መካከል ግጭትን በመፍጠር ጆርጅያ የተረጋጋ ማዕከላዊ መንግሥት እንዳይኖራት አድርጓል። በተለይ ከምርጫ ማግስት ምርጫው ተጭበርብሯል የሚሉ ቡድኖችን በማሰማራት አለመረጋጋቱ እንዲቀጥል ሆኖል። በሩሲያ ጣልቃ ገብነት ምክኒያት ጆርጅያ የማያባራ ጦርነት ውስጥ ለመግባት የተቃረበች አገር ሆናለች። በተለይ አብኻዚያ እና ኦስሺያ የሚኖሩበት አካባቢ የአናርኪስቶች መፈንጫ ሆኗል። ለስልጣን፣ ለጥቅምና ለበላይነት በሚደረግ ግብግብ ምክኒያት እነዚህ አካባቢዎች ሥርዓቱ ከድቶናል አግልሎናል ብለው እንዲያስቡ ተደርገዋል።
‹የአማራ ብሔርተኝነት› በሚል ስም በመራመድ ላይ ወዳለው አስተሳሰብ ስንመጣ ደግሞ ተመሳሳይ የሆኑ አካሄዶችን (patterns) እናገኛለን። ይህ እንቅስቃሴ ሲጀመር አማራ የሚባልን በሙሉ ያለውልና ያለአውድ በአንድ ዘንቢል የመጠርነፍ ዝንባሌ የነበረው ነው። ድርብርድብ ማንነቶችን ደፍጥጦ እንዲሁም ማንነት ማህበራዊ ውቅር (Social Construct) መሆኑን ሳይገነዘብ የተነሳ እንቅስቃሴ ነው። አጀማመሩ በዲያስፖራ ስለሆነ በተወሰነ ደረጃ መሬት ላይ ካለው ሀቅ ጋር የመለያየት እና በደረቅ ልፋፌ ላይ የመመርኮዝ አካሄድ ነበረው። መነሾው በትህነግ ላይ ያነጣጠረ ስለነበር ትህነግ ከሥርዓት ለውጥ በፊት ከአዲስ አበባ ቢነቀል ምን ሊፈጠር ይችላል ለሚለው በቂ ምላሽ አልነበረውም። እንቅስቃሴው በአብላጫው በስሜት የሚመራ በመሆኑ ከኢንስትሩሜንታሊዝም በተለዬ መልኩ ከነባራዊው ዓለም፣ ከአመንክዮ እና ከሜታፊዚክስ አስተምህሮ ቀድቶ እንቅስቃሴውን ለመጠበቅ ያስቀመጠው መርህ አልነበረም። በመሆኑም እንቅስቃሴውን የማስለቀሻና የተበዳይነት ትርክት መስበኪያ በማድረግ ሕዝቡን የሚያወናብዱ ኃይሎች ቢመጡ ‹ምን ይደረጋል› የሚል መውጫ (exit strategy) አልነበረውም፤ አሁንም የለውም።
ከምንም በላይ ደግሞ ይህ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ፍላጎቱ ሁሉንም የአማራ ሕዝብ ከፋብሪካ እንደወጣ ሳሙና ተመሳሳይ አስተሳሰብና ቀለም ለማልበስ የሞከረ ስለነበር ውድቀትን አምጥቷል፤ ብሔርተኝነቱ በውስጡ የግብረ-ገብነት እና የዲሞክራሲ ባህል ያልዳበረበት ስለሆነ ከአማራ ሕዝብ ባህል ጋር ሊጣጣም አልቻለም፡፡ የስድብን፣ አላዋቂነትን የማድነቅንና የተናካሽነት ባህል ለማስፋፋት በመሞከሩ ተደራራቢ ችግሮች ተፈጥረዋል። ከነባራዊ ሀቅ ጋር ያልተሳሰሩ ነገሮች ስለነበሩት ልዩነቶች እየጎሉ ሄደዋል፤ ልዩነቶች ሲፈጠሩ ቆም አድርጎ ለማረቅ የሚያስችል ልጓም ስላልተበጀለት ችግሮችን ከመቅረፍ ይልቅ ለፍረጃ፣ በጣም ሰቅጣጭ ለሆነ የስብዕና ገደላ፣ ግለሰባዊ የአስተሳሰብ ልህቀትን ከማበረታታ ይልቅ ለደቦ ድንቁርና ተጋላጭ ሆኗል። በልክ የለሽ ጥርነፋ፣ በአደገኛ ፍረጃ እና በደቦ የተጨማለቀ የተጠለፈ የማንነት ብሔርተኝነት ቁልቁል ሲምዘገዘግ ታይቷል።
ከምንም በላይ ግን የብሔርተኝነቱን ክፍተቶች ሲያጠኑ የነበሩ የቀድሞው ብአዴን/አዴፓ ሰዎች በቀላሉ ለስልጣን፣ ለጥቅምና ለበላይነት ትግል ሊጠቀሙበት ችለዋል። በዚህ ሒደት ውስጥ ስልጣንን ለረጅም ጊዜ ይዞ ለመቆየት በማሰብ በተሰላ መንገድ በአማራው ሕዝብ ውስጥ ክፍፍል እንዲፈጠር አድርገዋል። በተለይ ብሔርተኛ ነኝ የሚለውና በጭፍን ፈረስ ይጋልብ የነበረውን ማዕበል የሀሰት ትርክት በመጫን በአደባባይ ሀቅን ሸሽቶ ለሴራ ፖለቲካ ዘብ እንዲቆም አድርገውታል። ይህ መከፋትንና መከፋፈልን ፈጥሯል።
በዚህ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ የተሳተፉ የጎንደር ወጣቶች፣ ሊሂቃን እና ታጋዮች አብዛኞቹ ‹አማራ› ‹አማራ› በሚል ልባቸው እስኪወልቅ ሲጮሁ የነበሩና የብሔርተኝነት እንቅስቃሴው ፈተና ገጥሞት ለክፍፍል ሲዳረግ ተከድተናል የሚል የባዶነት ስሜት የፈጠረባቸው ሆነዋል። ይህ ስሜት በጎንደር ምስልቅል ውስጥ የራሱ ድርሻ ያለው እና አሁን ጎንደር ከተማ ለሚታየው ችግር ቀጥተኛ ባለሆነ መንገድ አበርክቶ ያለው ነው። [ነገሩ የበዛ በደል አለውና ዝርዝሩ ኪስ ይቀዳል]
(መ) የጎንደሬነት ሥነ–ልቦና መሸርሸር
በቅድሚያ ለዚህ ንዑስ ርዕስ ያለኝ ማሳሰቢያ ታሪክን መሠረት ያደረገ ነው። የጎንደሬነት ሥነልቦና እንዴት ያለ ነው ለሚል መልሱ ‹በሥነ-መንግሥት ግንባታ እና በውይይት ላይ የተመሰረተ› የሚል ነው። እናም የጎንደሬነት ሥነ-ልቦናን ስናስብ የታሪክ እርሾውን እያሰላሰልን እንዲሆን ይመከራል። በጎንደሬነት ሥነ-ልቦና ውስጥ ሦስት ነገሮች ጎልተው ይታያሉ፤ ሃይማኖተኛነት፣ ጀግና አወዳሽነት እና የአደባባይ ክርክር፣ ውይይትና ሙግት። በዛሬው የጎንደር ፖለቲካ እና መወድስ ውስጥ በስፋት ጎልቶ የሚንፀባረቀው የመካከለኛው ዘመን የጎንደር ገናና ታሪክ ነው። ይህ ታሪክ የሚጀምረው አጼ ሠርፀ ድንግል ወይና ደጋ ልዩ ስሙ ጉዛራ ላይ ቤተ መንግሥት ከሰሩ በኋላ እና ከሠርፀ ድንግል በኋላ የነገሠው አጼ ያዕቆብ በማያሻማ ሁናቴ የመንግሥቱን መቀመጫ ወደ ደምቢያ ካሻገረበት ጊዜ አንስቶ ነው። አጼ ሱስንዮስ ደንቀዝንና ጎርጎራን የመረጡ ቢሆንም ልጃቸው አጼ ፋሲል ጎንደር ላይ ቋሚ ቤተ-መንግሥት በመገንባት ጎንደር ከአሥራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ እስከ አሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ድረስ የመንግሥቱ አስተዳደር ማዕከል ሆኖ ዘልቋል። ሱስንዮስ ወደ መጨረሻ ዘመኑ ካቶሊክ ሆኖ መንግሥቱንም ካቶሊክ አድርጎ ነበር በዚህም ሕዝቡ ደስተኛ አልነበረም። ከእርሱ በኋላ ልጁ ፋሲለደስ ነግሶ ‹ካቶሊክ ትርከስ ኦርቶዶክስ ትንገስ!› ብሎ የመንግሥቱን ኃይማኖት ወደ ቀደመው ሁኔታ መልሷል። ጎንደር ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘመነ መሳፍንት መጀመሪያ ድርስ የጦፈ የኃይማኖት ክርክር ይደረግ ነበር፤ ሕዝቡ ውይይት የሚወድ፣ ሀሳቡን በአደባባይ የሚሞግት፣ ለዕውቀት ቀናዒነት ያለውም ነበር። ነገሥታትም በአካባቢው ለመወደድ ቶሎ
ብለው ቤተ ክርስቲያን ይሰሩ እና ሊቃውንትን ያከራክሩ ነበር።
አጼ ፋሲለደስ ከጎንደር ነገሥታት በእጅጉ የተሳካለት የተወደደ እና የገነነ ነበር። በንግሥናው ዘመን የፋሲል ቤተመንግሥትን በማሰራትናቀ ሌሎችም አርዓያውን እንዲከተሉ በማድረግ በአብያተ መንግሥታቱ ዘላለማዊ ቅርስ ጥሎ አልፏል። ፀጉረ ልውጥ በተለይ ነጮችን ከአገሬ ውጡልኝ በማለት በወሰደው የ Close-door- policy ይታወቃል። ለዛሬ አብሮነት ምሳሌ ሊሆን በሚችል መልኩ የጎንደር ሙስሊሞችን በእኩልነት አቅፎ አብሮነትን በተግባር አሳይቷል፡፡ በሰከነና ጥበብ በተሞላበት አስተዳደሩ የሚታወቀው አጼ ፋሲለደስ ለ36 ዓመታት ያህል ገዝቶ አልፏል። እርሱ ሲያልፍ ልጁ ጻዲቁ ዮሐንስ አዕላፍ ሰገድ ተክቶ ለአስራ አራት ዓመታት ያክል መቀመጫውን ጎንደር አድርጎ ገዝቷል። ጻዲቁ ዮሃንስ ኃይማኖተኛ እና ደግ ስለነበረ
“ጻዲቁ ዮሃንስ ዘውድ ይዞ ብቃት፣
ልበ አምላክ ሆነ ደግሞ እንደ ዳዊት፤
የደጉ ዮሃንስ ደግነት ቢነሳ፣
ዘሎ ባህር ገባ የተጠበሰ ዓሳ”
እየተባለ ይታወሳል።
ንጉሡ በኋላ ላይ ልጁን አቤቶ እያሱን አድያም ሰገድ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ› አሰኝቶ በመሾም መንኗል፤ ለምናኔ ያበቃው በባለቤቱ መከዳቱ ነው። አድያም ሰገድ በጎንደር የሚገኘውን ትልቁንና አስደናቂውን የደብረ ብርሃን ስላሴ ቤተ ክርስቲያንመ ያሰሩ የተወደዱ ንጉሥ ነበሩ። ደብረ ብርሃን ሥላሴ በድንቅ ሥዕሎቹ፣ በማይነቅዙ ውድ እንጨቶች በተሰሩ ቅርጻ ቅርጾቹ፣ በቀን እንደ ጸሐይ በሌሊት እንደ ጨረቃ በሚያበራ ጉልላቱ የሚታወቅ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን በኋላ ላይ ድርቡሽ ዘፍሮ አቃጥሎት ነበር። ጣሊያን ደግሞ በአውሮፕላን ደብድቦታል። ይሁን እንጅ እድሳት ተደርጎለት አሁንም ይገኛል፤ በአባ ኃይለ መስቀል ወልዱ የተሳሉት ስዕሎቹም አሁንም ማራኪና አስደናቂ ናቸው። አድያም ሰገድ ካኅንም ነበሩ።
“ወዴት ሄዶ ኖሯል ሰሞነኛ ቄሡ፣
ታቦት ተሸክሞ ዘውዱን ጥሎ እያሱ፤
ተሸሸገውን ያባቱን ቅስና፣
ገለጠው እያሱ ታቦት አነሳና፤
አየነው እያሱ ደብረ ብርሃን ቆሞ፣
ልክ እንደ ኩሩቤል ሶስቱን ተሸክሞ፤
ስላሴን ሲሸከም እያሱ ገነነ፣
ለአራቱ ኪሩቤም አምሥተኛ ሆነ።”
ተብሎላቸዋል።
ለ24 ዓመታት ገዝተዋል። የሳቸው ዘመን ማብቂያ የ17ኛው ክፍለ ዘመን ማለቂያ ነው። ከአዲያም ሰገድ ኢያሱ ቀጥሎ ባለው ጊዜ በይልጥ ደግሞ ከአጼ በካፋ ህልፈት በኋላ በተለያዩ ምክኒያቶች የጎንደር ገናናነት እየቀነሰ መጥቷል። ይሁን እንጅ ዝናውና መወድሱ ቀጥሏል። የገናናነቱ መቀነስ ስኹል ሚካዔል የተባለ የዐድዋ ትግሬ ዐይኑን ወደጎንደር ቤተ-መንግሥት ከማሳረፉ ጋር ይያያዛል፡፡ ይኼው የዐድዋ ትግሬ ገዥ ጎንደርን ከረገጠ በኋላ እ.አ.አ. በ1765 ልጁን ከእቴጌ ምንትዋብ ሴት ልጅ ከእሌኒ ጋር አጋባ፡፡ በ1767 ደግሞ እሱ ራሱ ሌላኛዋን የእቴጌ ምንትዋብን ልጅ አስቴርን አገባ፡፡ እህትማማቾቹን አባትና ልጅ አገቡ፡፡ ይህ ጋብቻ ጎንደርን የማውደም መወጣጫ መሰላል ፍለጋ ነበር፡፡ በጥቂት ዓመታት ቆይታው የእቴጌ ምንትዋብ የልጅ ልጅ የሆነውን የንጉሥ ኢዮአስን ሥርዓት አፍርሶ፣ ንጉሡን በሻሽ አሳንቆ ገደለው፡፡ ስኹል ሚካዔል የገደለው የሚስቱን ወንድም ነበር፡፡ በዘመኑ ንጉሥ መግደል ማለት የሀገር ሉአላዊነት የማፍረስ ያህል የሀገር ክህደት ተግባር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ እንግዲህ የጎንደር ቀዳሚው ቁልቁለት እዚህ ግድም ይጀምራል፡፡ እዚህ ላይ የትግሬ ልሂቃን በጎንደር ላይ ያላቸው ጥላቻና የክህደት ታሪካቸው ሁለት መቶ ሃምሳ ዓመት የሚሻገር ስለመሆኑ ልብ ይሏል፡፡ ይህን ጉዳይ ከሥልጣን ጋር ብቻ ሳይሆን በዋናነትነ ከሥነ-መንግሥት ባህሪ ልዋጤ አንፃር ሊታይ ይገባል፡፡ የጎንደር የውይይት የክርክር ባህል የተሸረሸረው በዘመነ መሳፍንት ዋዜማ ነበር፡፡ ዋዛማውን የከፈተው ደግሞ በጆን አቢንክ አገላለጽ “He was a ruthless and cold-blooded power politician….. He was not a ruler with political vision beyond control and self-interest.” የተባለለት ስኹል ሚካዔል ነበር።
ወደቀደመ ፍሬ ነገራችን ስንመለስ ከአጼ ኢዮአስ ህልፈት በኋላ ሥርዓት አልበኝነት እያዬለ ሄዶ ዘመነ-መሳፍንትን ወልዷል። በዘመነ መሳፍንት ወቅት የኃይማኖት ዕውቀት ክርክር እና የፍትሕ ርትዕ ክርክር እያሽቆለቆለ ሄዷል። በኋላ ላይ የዘመነ-መሳፍንትን ማብቂያ ያበጁለት ገናናው አፄ ቴዎድሮስ ዘመናዊነትን የሚያልሙና ሕግና ሥርዓት እንዲከበር አጥብቀው የሚመኙ ስለነበር ቤተ-ክርስቲያንን በተመለከተ ለአገልግሎት ከአምሥት ካህናት በላይ አያስፈልግም በማለታቸው የክርክሩና ውይይቱ ጉዳይ ይበልጥ እየቀነሰ ሄዷል። ከአጼ ቴዎድሮስ ህልፈት በኋላ በጎንደር የውይይት፣ የክርክርና የዕውቀት ልህቀት የበለጠ እያሽቆለቆለ ሄዷል። ባለፉት ሦስት መቶ ዓመታት የታሪክ ዥረት ውስጥ ጎንደር ከከፍታዋ ቁልቁል ወርዳ እግርጌው ላይ ወድቃለች፤ በሂደቱ ባጋጠሙ ምስቅልቅሎች ከ Center of Excellence ወደ Center of Anarchism አቅጣጫ እየሄደች ነው። ራዕይ በሌላቸው ካድሬዎች የምትታመስ መሆኗ ሕዝቡ ሥርዓት ጠል እንዲሆን አድርጎታል ስንልም በዚህ መነሻ ነው።
አሁን ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታ ብናየው ጎንደር ከጥንታዊው የጎንደሬነት ሥነ-ልቦ በጣም በረጅም ርቀት ላይ እንደሚገኝ መታዘብ እንችላለን። ለምሳሌ ሰሞኑን ከጎንደር ከተማ ከንቲባ ሹመት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ሀሳቦች ጥልቀት የሚጎድሏቸውና ዕውቀት በሌላቸው ሌጣ ካድሬዎች የሚዘወሩ ሆነው እናገኛቸዋለን። በጥንቱ ጊዜ በጎንደር አደባባዮች ውይይቶች፣ ሙግቶችና ክርክሮች የሚደረጉበት ዋነኛ ምክኒያት ሕዝቡ በማኅበራዊ ጉዳዮች ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ እንዲችል፣ በዕውቀት የነጠሩ ሊቃውንት ወደፊት እንዲመጡ፣ ንገሥታቱ በሕዝቡ ላይ ማናቸውንም (በተለይ የሐይማኖት) አስተምህሮቶች መጫን የማይችሉ መሆናቸውን ለማሳየትና በሕዝብና በመንግሥት መካከል ቅርርብን ለመፍጠር ነበር። በአሁኑ አጠራር ይህ በጣም ሊበራል ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ጋር የሚቀራረብ ነው።
ዛሬ ላይ ጎንደር የአደባባይ ክርክር፣ ውይይት፣ ሙግት የለም። ጎንደር አንድነቱ አደጋ ላይ ወድቆ፣ በስድስት ዞኖች ተከፋፍሎ፣ አንዱ ዞን ከሌላው ጋር በመሠረተ ልማት እንዳይተሳሰር እና በአካባቢዊ የጋራ ጉዳይች እንዳይገናኝና ለክልል እንዲገብር ተደርጎ፣ ከክልል የሚሾሙ በየዞኑ ያሉ ካድሬዎች ሕዝቡን እንዲጫዎቱበት ሆኗል፡፡ አጠቃላይ በተሳከረ ሥርዓት ውስጥ ይገኛል። ጎንደሬነት እንደ ጥንቱ ቢሆን ኖሮ ይህንን መሳከር ሀቀኛ ውይይት፣ ሙግትና ክርክር በማድረግ ለመፍታት ይሞከር ነበር። አሁን ግን በሚያሳዝን መንገድ የጎንደር ይዞታ ቁልቁል ሆኗል። በዚህ የቁልቁለት ጉዞ ውስጥ የተወሰኑ ወጣቶች በማወቅም ባለማወቅም አብረው ሲነጉዱ ይታያል።
ለማሳያነት ሰሞኑን በጎንደር ከንቲባ ሹመት ላይ የሚነሱ ሁለት ደከም ያሉ ክርክሮች ማስተዋል እንችላለን። አንደኛው ጎንደር ከተማ ላይ ጎንደር ከተማ ተወልዶ ያደገ መሾም አለበት የሚል ነው። ሁለተኛው ለጎንደር ከተማ ከንቲባ የሚሾመው ድርጅታችን ብልጽግና እንጅ ፌስቡክ አይደለም የሚል ነው። ሁለቱም ጎንደር ገናና ናት፣ ጥንታዊት ናት፣ ታሪኳና ከፍታዋን የሚመጥን መሪ ትሻለች ይላሉ።
የሁለቱም የጋራ ችግር የጎንደርን ገናናነት ያምኑና ለዚህች ገናና ከተማ መሪ ሆኖ እንዲሾም ጥያቄ የሚያቀርቡት ግን ከሚሰብኩት ሥልጣኔ፣ ገናናነት፣ ጥንታዊነት፣ ከፍታ ፍፁም በተቃራኒ መልኩ በክልል ሰዎች የተሾመ ተላላኪ እንዲላክላቸው ነው። በሕዝብ ያልተመረጠ ማንኛውም ተሿሚ የሿሚዎቹን ፍላጎት የሚያሟላ ተላላኪ መሆኑን መገንዘብ አቅቷቸዋል።
በጎንደር ገናናነት፣ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ከፍታ ልክ የሚሆነው በግልፅ ክርክር፣ ውይይት፣ ሙግትና በሕዝብ ምርጫ ከንቲባ እንዲመረጥ ሲደረግ ነው። ትግልም መደረግ ያለበት እንዲህ ዓይነት ሥርዓት እንዲመጣ በማድረግ ላይ ነበር። በመሆኑም ‹ጎንደር ሕዝብ ባልመረጠው ሰው መተዳደር አይገባትም› ብሎ ገፍቶ መታገል ይገባል (በነገራችሁ ላይ ዞን የሚባለውን መዋቅር “ሕገ መንግሥቱ” አያውቀውም፤ “ሕገ-መንግሥቱ” ያላወቀውን ምርጫ አያወቀውም)።
በሰለጠነው ዓለም የትኛውም የአስተዳደር ቢሮ ውድድር ተደርጎበት ነው መሪ የሚያገኘው። ኢትዮጵያ ግን በወያኔ ሰነድ ምክኒያት ሥልጣን በሙሉ በሹመት በመሆኑና ተሿሚዎች ለሿሚዎች የሚሰግዱበት ኔትወርክ ያለ በመሆኑ በታችኛው የመንግሥት እርከን ያሉ ኃላፊዎች ወደው ሳይሆን በአሰራሩ ደጋፊነት ችግር ፈጣሪዎች ይሆናሉ። እንደ ጎንደር ባለ መልከ ብዙ መገፋት በአለበት አካባቢ ደግሞ ሥርዓት አልበኝነት ወይም አናርኪዝም እንዲስፋፋ ነገሮች ምቹ ይሆናሉ።
ጎንደር ከተማን በከንቲባነት ተሹሞ መምራት ያለበት ጎንደር ተወልዶ ያደገ ነው የሚሉት ደግሞ ወደተሳሳተ አቅጣጫ መንጎዳቸውን ያላወቁ ናቸው። የጎንደር ከተማ የመላው ጎንደሬ መናገሻ ናት፤ ከወልቃይት እስከ ጋይንት፣ ከቋራ እስከ ደራ፣ ከበየዳ እስከ ስማዳ፣ ከመተማ ጠረፍ እስከ ተከዜ ጫፍ የሁሉም ጎንደሬ መማፀኛ ከተማ ናት።
እንደ ጥንቱ ጎንደሬው (በስሜን በጌምድር) አንድ አስተዳደር ስር ቢሆን ኖሮ ለዚህች ከተማ ከንቲባ መመረጥ የነበረበት ከሁሉም የጎንደር ክፍል ተወዳዳሪዎች በአደባባይ ውይይት፣ ሙግትና ክርክር አድርገው ሕዝብ ድምፅ ሰጥቷቸው ነበር። አሁን ግን የአስተዳደር ሥርዓቱ ሌላ ስለሆነ እና የጎንደር ከተማ እና አካባቢው ራሱን የቻለ ዞን ስለሆነ በዚህ ዞን ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች ከየትም ይምጡ፣ የትም ይወለዱ ለሚኖሩበት ከተማ አስተዳዳሪ ሆነው መመረጥና ማገልገል መብታቸው ይገባል፤ ጎንደርን የሚመጥነው አስተሳሰብ ይኼ ነበር። ቁልፉ ነገር ተሿሚ ሳይሆን ሕዝብ የመረጠው ይምራን የሚለውን መርህ መከተሉ ላይ መሆን ይኖርበታል።
የቀድሞ ወያኔ የዛሬ ብልጽግና ካድሬዎች ድርጅታችን ይሾምልናል ፌስቡክ አያገባውም የሚሉትን ከማስረዳት ቢቻልም ከድንቁናቸው አንጻር ሊገባቸው የማይችል ተላላኪዎች ስለሆኑ በተራዘመ ትግል ከመሪነት ቦታ ከማስወገድ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለም። በጥልቅ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ ግን ከደሥርዓት ጠልነት ወደሥርዓት ባለቤትነት መሸጋገር ስለሚቻልበት መሠረታዊ የሕዝብ ባህሪ ነው! ትህነግን እየደመሰስን ዘላቂ መፍትሔ ማንበር የትውልድ ዕዳ ነው!!
—
ተፈፀመ።
ባየ ተሻገር
ጥቅምት 2014 ዓ.ም