የአፋር ክልል በህወሓት ተወስዶብኝ የነበረውን መሬት አስመለስኩ አለ

by RAS Media

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “በሽብርተኝነት” የተፈረጀው ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረባቸው ያለፉት ሶስት አስርት ዓመታት “ያለ አግባብ ተወስዶብኝ ነበር” ያለውን አንድ ቀበሌ አሁን በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ማስተዳደር መጀመሩን የክልሉ ጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ ሻለቃ ኢብራሒም ሑመድ ለዋዜማ ራዲዮ ተናግረዋል።
“ሳውኔ” የምትባለዋ ይህቺ ቀበሌ በአፋር ክልል ዞን ሁለት፣ ዳሎል ወረዳ እና በትግራይ በማዕከላዊ ትግራይ ዞን በሳጺ ጸዓዳ አንባ ወረዳ መካከል የምትገኝ ናት። ቀበሌዋ አፋርኛም ትግርኛም የሚነገርባት ሲሆን አሁን የአፋር ክልል መንግስት የአስተዳደር መዋቅር ዘርግቶ ማስተዳደር መጀመሩን ሻለቃ ኢብራሒም ነግረውኛል በማለት ዋዜማ ራዲዮ ዘግቧል።
ሳውኔ የምትባለው ቀበሌ ሸክ አደም ቡራ እና ካላክ በመባል የሚታወቁ አካባቢዎች ያሉባት ሲሆን አብዛኛው የአካባቢው አየር ሁኔታ ደጋማ የሚባል ነው። ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ በትግራይ ክልል በማዕከላዊ ዞን በሳጺ ጸዓዳ አንባ ወረዳ ስር ስትተዳደር ነበር።
የቀበሌው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ የማንነት ጥያቄ በማንሳት በአፋር ክልል ውስጥ እንተዳደር የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን ያነጋግርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተውኛል በማለት ዋዜማ በዘገባው አካቷል።

You may also like